ቭላድሚር ፑቲን ማን ነው?
- Dawit Eyayu
- Oct 7, 2015
- 2 min read

የሩስያው ፕሬዚደንት በአሸባሪው ISIS ላይ ቆርጠው ተነስተዋል። ባለፈው ሳምንት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባ ላይ ቁጣ የተቀላቀለበት ንግግር ያደረጉት ፑቲን ቃላቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ ቀናት አልፈጀባቸውም። ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሰብአዊ ፍጡራንን አንገት በካራ እየቀላ፣ በእሳት እያጋየና ከህንጻ ላይ እየወረወረ በቪድዮ በመቅረጽና ፎቶ እያነሳ በማህበራዊ ድህረ ገጾች የሚለቀውን እንዲሁም በሲሪያ ብዙ የሽብር ድርጊት በመፈጸም ላይ ያለውን ISISን ጠራርጎ ለማጥፋት ፑቲን ቃልገብተዋል! ለዚህም ጎዞ ጀምረዋል። ቭላድሚር ፑቲን በዚህ ረገድ አሜሪካንን በገሀድ የወቀሱና ይህንን አሸባሪ ቡድን ለመዋጋት የወሰደችውን የተለሳለሰ አቋም ከሌሎች ፖለቲካዊ ውዝዋዜዎቿ ጋር በማቆራኘት አብጠልጥለዋል። ለመሆኑ ፑቲን ማን ናቸው? እ.ኤ.አ 1999 የወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት የነበሩት ቦሪስ የልሲን የወቅቱን ጠቅላይ ሚኒስትር አባረው በምትኩ የኬጂቢ ኦፊሰር የነበሩትን እኚህን ሰው ሾሙ። በዝያው አመት በህመም ምክንያት ወደ ሆስፒታል ይመላለሱ የነበሩት የልሲን የፕሬዚደንት ስልጣናቸውን ለፑቲን አስረክበው ተሰናበቱ። ፑቲን በ2004 እንደገና ተመርጠው ፕሬዚዳንት ሆኑ። በ2008 ለፕሬዝደንትነት ሳይወዳደሩ ቢቀሩም ወደ ቀድሞው የጠቅላይ ሚንስትርነት ስልጣናቸው ተመለሱ። በ2012 ምርጫ ደግሞ ወደ ፕሬዚደንትነታቸው ተመለሱ። በዚህ ጊዜ ለኖቤል ሽልማት እጩ ሆነው ቀርበው ነበር። በ1952 የተወለደው ፑቲን በ1975 የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ የኬጂቢ ሰራተኛ በመሆን በምስራቅ ጀመርመን ስራውን ጀመረ። በዝያም እስከ 1989 አገለገለ። የሶቭየት ህብረት መንግስት በ1991 ሲወድቅም ፑቲን በኮለኔልነት ማእረግ በጡረታ ተገለለ። ነገር ግን በዝያው አመት የሊበራልአስተሳሰብ አራማጅ የነበረውን አንቶኒዮ ሶቦቻክ በውጭ ግንኙነት ለማገልገል ስራ ጀመረ። እንዲህ እንዲህ እያለ በሞስኮና ሌሎች ከተሞች በማገልገል የቦሪስ ዬልሲንን እይታ ስቦ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማእረግ መጣ። ስለ ኦርቶዶክስ እምነቱ በግልጽ የሚናገረው ፑቲን በሀይማኖቱ ተቀባይነት የሌላቸውንና ምእራባውያን ሀገሪቱ እንድትቀበላቸው የሚያስገድዱ ብዙ ህጎችን በይፋ በመቃወምና በሀገሪቱ ውስጥ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው በማድረጉ ብዙ ወቀሳ ይቀርብበታል። ከዚህም አንዱና ዋንኛው የግብረሰዶማውያን ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ ፑቲን ግልጽ አቋሙን በማስቀመጥ በሀገሩ ይህን አይነት ተግባር የሚፈጽሙትን እንደማይታገስ አሳውቋል። በዚህም ባለፈው አመት በሩስያ የተደረገው የሰመር ኦሎምፒክ ላይ ከተለያዩ ሀገራት የገቡ ግብረሰዶማውያን ከፍተኛ ተቃውሞቢያደርጉም ፑቲን "ገብታችሁ እስክትወጡ አስፈላጊውን የጸጥታ ጥበቃ እናደርግላችኋለን ነገር ግን ግብራችሁን እዚህ አትፈጽሙም" በማለት ተከላክሏል። ይህም በሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ዘንድ ትችትን አስነስቶበታል። ከሁለት ሳምንት በፊት ደግሞ እንዲሁ አሜሪካና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት "የእንሣትንና እጽዋትን ህዋሳት በላቦራቶሪ በማዳቀል" የሚያመርቱትን ምግቦች (ጄሞ) ወደ ሀገሬ አላስገባም፤ በሀገሬም አይመረትም በማለት ማእቀብ ጥሏል። "እነዚህ ምግቦች በተፈጥሮ ላይም ሆነ በተፈጥሯዊው ሰው ላይ የሚያሳድሩትን ችግር እንረዳለን። በመሆኑም እኛም አናመርትም የተመረቱትም ወደ ሀገራችን አይገቡም!ህዝባችንን ተፈጥሯዊ ምግቦችንን እንጂ አርተፊሻል ምግብ አንመግብም" ሲል ተናግሯል። ፑቲን የሁለት ሴት ልጆች አባት ነው። ለመሆኑ ፑቲን አለምን በማሸበር ላይ ባለው ISISን ለመዋጋት ወደ ሲሪያ ያደረገው የጦርነት ጉዞ ይሳካለት ይሆን?
(የትነበርክ ታደለ)
Comments